Publications

ፀጥታ እና ቁሳቁስ-- ዩቫስኪላ እና አዲስ አበባ

ኤልያስ ይትባረክ አለማየሁ (ዶ/ር)

የምኖረው በሀገሪቱ ዋና ከተማ በአዲስ አበባ ነው፡፡ መሃል ፒያሳ ላይ የሚገኘው የምኖርበት አፓርትመንት ከሥሩ የተጨናነቀ መስቀለኛ መንገድን ይማትራል፡፡ በመስኮቴ የማየው የዕለት ተዕለት ትርዒት የትራፊክ መጨናነቅ፣ የማያቋርጥ የእግረኞች ፍሰት፣ ጥጉን ይዘው የተኮለኮሉ ጫማ ጠራጊዎች፣ መኪና የሚያጥቡ ወጣቶች፣ የመኪና ማቆሚያ ሠራተኞች፣ የኔቢጤዎች፣ የጎዳና ላይ አዋካቢዎች፣ ሱቅ በደረቴዎች፣ የጥበቃ ሠራተኞች፣ ባለቤት አልባ ውሾችና  ጀብራሬዎችን ያጠቃልላል፡፡ በሥራ መግቢያና መውጫ ሰዓት መንገዶቹ ያለማቋረጥ ጥሩንባቸውን በሚያንባርቁ መኪኖች ሙሉ በሙሉ ይጨናነቃሉ፡፡ ፋታ የሌለው፣ ምስቅልቅሉ የወጣ፣ ሞገደኝነት የጎላበት፣ አንዳንዴም ሕልም መሠል የሆኑ እንቅስቃሴዎች የሰፈኑበት መስቀለኛ መንገድ ነው፡፡

በ2006 እና 2007 ዓ.ም በፊንላንዷ ከተማ ዩቫስኪላ በተለያዩ ጊዜያት በአጠቃላይ ለአምስት ወራት ቆይቼ ነበር፡፡ በመጀመሪያው ጉዞዬ፣ በአጋጣሚ ልክ እንደ አዲስ አበባው ቤቴ፣ መሐል ከተማ መስቀለኛ መንገድ ላይ ባለ አፓርትመንት ነበር የቆየሁት፡፡ ሆኖም ትዕይንቱና ድምጾቹ ከአዲስ አበባው አፓርትመንቴ ስር ከሚገኘው መስቀለኛ የመኪና መንገድ በእጅጉ የተለየ ነበር፡፡ በጣም የተለመዱት ድምጾች ከትራፊክ መብራት የሚወጡት በየደቂቃው የሚሰሙ ለዐይነስውራን የሚለቀቁት “ጢጥ ጢጥ” የሚሉ ድምጾችና እነሱን ተከትለው እየቆሙ የሚያልፉት ጥቂት መኪኖች ናቸው፡፡ በዩቫስኪላው የአፓርትመንት መስኮት፣ ባገኘሁት አጋጣሚ ሁሉ መስቀለኛው መንገድ ላይ ያሉትን እንቅስቃሴዎች በንቃት ስከታተል ነበር፡፡ በየዕለቱ ጠዋት በእጁ ፌስታል የያዘ ሰው በመስቀለኛው መንገድ ማዕዘን ላይ ወደምትገኝ አነስተኛ ሱቅ ይመጣል፡፡ ሰውየው ወደ ሱቁ ይገባና ጥቂት ቆይቶ ይወጣል፡፡ ከዛም ከኪሱ የታሸገ የቆርቆሮ ቢራ ያወጣና ከሱቁ ዘወር ብሎ በሚገኝ ቦታ ላይ ቆሞ ይጠጣል፤ ቀጥሎ ሲጃራ ያጨስና ተመልሶ ወደ ሱቁ ይገባል፡፡ ይህንን ተግባር በየዕለቱ ጠዋት ሦስት አራት ጊዜ ይደጋግመዋል፡፡ አንዳንዴ ከሦስተኛው ወይንም አራተኛው ቢራ በኋላ ወደአጥሩ ዞሮ ይሸናና ወደ ሱቁ ይገባል፡፡ ይህንን ተግባር ሳያዛንፍ በተወሰኑ ጊዜያት መሀል በየጥዋቱ ይፈጽመዋል፡፡

በምስቅልቅል ዕይታና በማያቋርጥ ጫጫታ ከተሞላው ከአዲስ አበባው መስቀለኛው መንገድ ጋር ሲነፃፀር፣ የዩቫስኪላው ረጃጅም ፀጥታዎችና አጫጭር ድምጾች የሚፈራረቁበት፣ ድምጾቹም የሚደጋገም ምት ያላቸው ወደ አሰልቺነት የሚጠጉ ናቸው፡፡ በየዕለቱ ጠዋት እዛች ሱቅ ላይ የሚመላለሰው ሰውዬ የሚከውነው ተግባር ተመሳሳይ ነው፡፡ ውጪ ሆኖ ቢራውን ለመጠጣትና ሲጃራ ለማጨስ የሚያጠፋው ጊዜ ሱቅ ውስጥ ከሚያሳልፈው ጊዜ ጋር ሲነፃፀር አጭር ነበር፡፡ ”ጢጥ ጢጥ“ የሚለው ከትራፊክ መብራቱ የሚወጣው ድምጽና ከመኪናዎቹ የሚወጡት ድምጾች የሚሰሙት በሰፊ የዝምታ ዳራ ውስጥ ነው ፡፡ አብዛኛው ሰው ቤት ውስጥ በሚቆይበት ከተማ፣ አልፎ አልፎ መስቀለኛውን መንገድ ከሚሻገሩ ጥቂት እግረኞች በቀር መስቀለኛው መንገድ ላይ የሚታየው በየጠዋቱ ወደ ሱቁ የሚመላለሰው ሰውዬ እንቅስቃሴ ብቻ ነበር፡፡ ይህ ትዕይንት ፋታ በሌለው ጫጫታ ውስጥ፣ ፀጥታ በሚናፈቅበትና አብዛኛው ሰው ቀኑን ውጭ መንገድ ላይ ከሚያሳልፍበት ከአዲስ አበባው ትዕይንት ጋር ሲነጻጸር ፍጹም ተቃራኒ ነው፡፡


በተጨማሪ በዩቫስኪላ ትኩረቴን የያዘው በብዛት የሚገኙት ባዶ ቦታዎች፣ ሐይቆችና ደኖች ናቸው፡፡ በዩቫስኪላ ከተማ እያንዳንዱ ቤተሰብ ጥቂት ተጉዞ ሐይቆችንና ደኖችን ማግኘት ይችላል፡፡ ከከተማ ፕላን አንጻር የዩቫስኪላ ከተማ ግንባታ በሰፋፊ ደኖች ውስጥ የሚገኝ ነጠብጣብ ነው፡፡ በተቃራኒው የአዲስ አበባ አረንጓዴ ሥፍራዎችና ባዶ ቦታዎች በከተማው ሰፊ ግንባታ ውስጥ የሚገኙ ነጠብጣብ ናቸው፡፡ እየቆየሁ ከመስኮቴ አሻግሬ በሁለቱም ከተሞች የታዘብኩት ግንባታና ባዶ ቦታዎች ያላቸው ግንኙነት፣ ከዩቫስኪላና አዲስ አበባ ነዋሪዎች ባህርይ ጋር እንዴት እንደሚያያዝ ማሰብ ጀመርኩ፡፡ እንደ ነዋሪ ግዑዙ ከተማ የኛን ማንነት የሚገልጽ ነው፡፡ “መጀመሪያ እኛ ሕንፃዎቻችንን እንገነባለን፤ ቀጥሎም ሕንፃዎቻችን እኛን ይገነቡናል” እንዲሉ፡፡

ነገሮችን በደምሳሳው የማየት ችግር እንዳለ ሆኖ፣ ፊንላንዳውያን ብዙ ጊዜ የሚታወቁት ለፀጥታ ባላቸው ፍቅር ነው፡፡ ከአንዲት አፍሪካዊት ከተማ እንደመምጣቴ ይህንን በቀላሉ መታዘብ ችያለሁ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከፊንላንዳውያን ጋር በነበረኝ ቆይታ፣ ለመናገር ተብሎ ብቻ የሚነገር ነገር ወይም ለማውራት ተብሎ ብቻ የሚወራ ወሬ፣ በአጠቃላይ ዝም ላለማለት ሲባል ብቻ የሚወረወሩ ንግግሮች [small talk] እንደሌሉም መታዘብ ችያለሁ፡፡ በፊንላንድ ዝምታ የጭውውት አካል ነው፡፡ ቃላት መልዕክቶችን ለማስተላለፍ ያገለግላሉ፡፡ ለቃላት ክብር አለ፤ ከሰዎች ጋር ሆኖም ዝም ማለት ይቻላል፡፡ ዝምታን የሚገነዘቡት እንደ ጫጫታ አለመኖር ሳይሆን የጭውውቱ አካል አድርገው ነው፡፡ ይህን ሁኔታ በዩቫስኪላ ከተማ ቆይታዬ ያጋጠሙኝ የሚከተሉት ገጠመኞች ሊገልጹት ይችላሉ፡፡

በዩቫስኪላ ቆይታዬ ባንድ ግብዣ ላይ ለመገኘት ወደ ግብዣው ቦታ እየሄድኩ ነበር፡፡ በመንገዱ ላይም ቀደም ብሎ የማውቃት አንዲት ፊንላዳዊት ከሁለት ልጆቿ ጋር ወደ ግብዣው ስትሄድ ተገናኘን፡፡ የተለመደውን ሠላምታ ከተለዋወጥን በኋላ ዝምታ ሆነ፡፡ ዝምታውን ለማስወገድ በመሞከር “አሁን የምንሄድበትን ቤት አድራሻ ስመለከት የሠፈሩ መንገዶች በሙሉ የተሰየሙት በዳንስ ስሞች ነው፡- ታንጎ፣ ዋልዝ፣ ሩምፓ እና የመሳሰሉት” አልኳት፡፡ እሷም “አዎ፤ በአንዳንድ የዳንስ ዓይነቶች” አለችኝ፡፡ እንደገና አጭሯ ምልልሳችንን ዝምታ ተከተላት፡፡ ሌላ ቀለል ያለ ጭውውት ለመቀጠል በማሰብ “የሠፈሩ ነዋሪዎች ወይ ዳንስ ይወዳሉ፤ ወይንም ዳንሰኞች መሆን አለባቸው” አልኩኝ፡፡ የመለሰችልኝ ግን ቀልዴን በመረዳት ሳይሆን በቁምነገር ነበር፡፡ “አይደለም፤ እዚህ ሠፈር እኔም እኖር ነበር፤ የመንገዶቹ ስሞች የተሰየሙት ኗሪዎቹ ዳንስ ስለሚወዱ አይደለም” አለችኝ፡፡ ራሴን ማስታወስ ነበረብኝ፡- “ለመናገር ብቻ ብለህ አትናገር!” ከጥቂት ዝምታ የወደቀባቸው እርምጃዎች በኋላ ወደ ግብዣው ቦታ ደረስን፡፡

ሌላው አጋጣሚ ደግሞ፣ አንድ ፊንላዳዊ ጓደኛዬን በአፓርትመንቴ ሻይ ጋብዤው የሆነው ነው፡፡ በቅርቡ ለጥቂት ቀናት ከከተማ ውጭ እንደተጓዘ አውቅ ነበር፡፡ ስለዚህ ወደ ቤቴ ከደረሰ በኋላ፣ ዝምታውን ለመግፈፍ በማሰብ “ጉዞህ እንዴት ነበር?” ብዬ ጠየኩት፡፡ ይህ ዓይነቱ ጥያቄ ለኢትዮጵያውያን ብዙም አትኩሮት ያለው መልስ ባለመጠበቅ ጣል የሚደረግ፣ እንዲሁም ዝምታን ለማስወገድና ሊቀጥል ለሚችል ጭውውት መንደርደሪያነት የሚሰነዘር ነው፡፡ ከጓደኛዬ ያገኘሁት መልስ ግን በቁምነገር የተሞላ የጉዞው ትረካ ነበር፡፡ ከትንሽ አትኩሮት የተሞላበት ዝምታ በኋላ የጎበኛቸውን ቦታዎች፣ በእያንዳንዱ ቦታ ላይ የፈጸማቸውን ተግባራት፣ ያገኛቸውን ሰዎች ዓይነትና በጉዞው የሸፈነውን ኪሎሜትር በጥንቃቄ ዘረዘረልኝ፡፡ የጉዞ ዘገባውን ካዳመጥኩ ቦኋላ ለመጠየቅ ብቻ ብዬ መጠየቅ እንደሌለብኝ ለራሴ ደጋግሜ ነገርኩት፡፡- በፊንላንድ ምድር ዝም ላለማለት ብቻ ተብሎ የሚደረግ ንግግር የለም! [No Small Talk!]

ከዚህ በተቃራኒ አዲስ አበባ ውስጥ ዝምታ ያቁነጠንጣል፡፡ በኢትዮጵያ ባህል በተለይ በእንግዳ ፊት ዝም ማለት ከጨዋነት የራቀ ነው፡፡ አሁንም አሁንም ማጫወት ይጠይቃል፡፡ የሠላምታ ልውውጥን የመሰለ ቀላል ነገር የተለመዱ ቃላትን በመደጋገም ብቻ ያለማቋረጥ ለደቂቃዎች ሊካሄድ ይችላል፡፡ ከተማዋ በተለይም ደግሞ የከተማዋ ማዕከል ከሰዎች፣ ከተሽከርካሪዎች፣ ከእንስሳት፣ ከእምነት ቦታዎች፣ ከሙዚቃ መሳሪያዎችና ከመሳሰሉት በሚወጡ ድምጾች ያለዕረፍት ታላዝናለች፡፡ እፎይ የሚባልበት የጥሞና ቦታ ለማግኘት ያዳግታል፡፡

ከላይ የተገለፀው ትዝብት እንዴት ወደ ከተሞች ሁኔታ ሊተረጎም ይችላል? እዚህ ላይ ባንድ በኩል ዝምታን (ባዶ ቦታዎችን) ይዘን በሌላ በኩል ደግሞ ጫጫታን (ቁሳቁስን ወይም ሕንፃዎችን) አስቀምጠን ማነጻጸር ይቻላል፡፡ ባዶ ቦታዎች ወይንም በሕንፃዎች መካከል ያሉ ክፍተቶች ከዝምታ ጋር ያላቸው ግንኙነት ከውክልና ባለፈ ከጠቀሜታ አንፃር ማየት ያስፈልጋል፡፡ በቁሳቁስና ከመንገዶች በሚመነጩ ጫጫታዎች መካከል ያለው ግንኙነትም እንደዚሁ ነው፡፡ እዚህ ላይ “ቁሳቁስ” የሚለው ቃል በዋናነት የሚወክለው የከተማን አውድ ግምት ውስጥ ሳያስገቡ፣ ማለትም መንገዶችንና ባዶ ቦታዎችን ሳይወስኑ፣ የአየር ንብረቱንና የነዋሪዎቹን ሁኔታ ሳያገናዝቡ የተገነቡ ሕንፃዎችን ነው፡፡

የፊንላንዳውያን ዝምታ ለባዶ ቦታዎች፣ ለሐይቆችና ለደኖች ባላቸው ፍቅር የተገለጸ ይመስለኛል፡፡ የተመጠነ ንግግራቸውም በሰፊ ደን መሐል በሚገኙት ትናንሽ የሕንፃዎችን ስብስብ ሊገለጽ ይችላል፡፡ በተቃራኒው በቋሚነት የሚሰማው የአዲስ አበባ ጫጫታና ግርግርም በተገኘው ባዶ ቦታ ሁሉ ቁሳቁስ በማኖር ፍቅር ይገለፃል፡፡ ከተማዋ ያሏት ጥቂት የሕዝብ ባዶ ቦታዎችና መናፈሻዎች ቁጥር ከሚጠበቀው ደረጃ እጅግ ያነሰ ነው፡፡ የከተማዋን እያንዳንዷን ጥግ በሰው ሰራሽ ነገሮች ለማጨቅ እሽቅድምድም ነው፡፡ ባዶ ቦታዎች እንደ ባከኑ መሬቶች ተደርገው ነው የሚቆጠሩት፡፡ ሆኖም በሥርዓት የተገነባ ከተማ ማለት የሕንፃዎችና በነሱ መሐል ያሉ ክፍት ቦታዎች ቅንብር ሲሆን፣ የሁለቱም ተገቢ ምጣኔ አስፈላጊ ነው፡፡ ወደ ውስጥና ወደ ውጭ በመተንፈስ፣ በዕረፍትና በእንቅስቃሴ፣ በተግባርና በማሰላሰል መካከል የሚያስፈልገውን ሚዛን መጠበቅ አስፈላጊ ነው፡፡ ሰዎች ወደውስጣቸው የሚያዩበትና ራሳቸውን የሚያደምጡበት የጥሞና ጊዜ ይፈልጋሉ፡፡ ይህ ግንዛቤ ከተሞች የሕንፃና የቁሳቁስ ስብስብ ብቻ ሳይሆኑ የሥነ ልቦናንና የመንፈስ ፍላጎት የሚያረኩ ቦታዎች አድርገን እንድናይ ይጋብዘናል፡፡

የአዲስ አበባ የከተማ ዲዛይን ትኩረት በቁሳቁስ (በሕንፃዎች) መካከል ባለው ክፍት ቦታ ሳይሆን በራሳቸው በቁሶቹ ዲዛይን ላይ ነው፡፡ ነገር ግን በቁሶች ስብስብ ብቻ ለኑሮ አመቺ የሆነች ከተማ መፍጠር አይቻልም፡፡ ከተማዋ ከብዙ ዓመታት ጥልቅ እንቅልፍ በኋላ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ እየተቀየረች ነው፡፡ ዳግም ወደነበረችበት ሁኔታ በማትመለስበት መልኩ የመንገዶች ግንባታ፣ ሰማይ ጠቀስ ፎቆችና የኮንዶሚንየም ቤቶች ከተማውን አዲስ አድማስ እያጎናፀፏት ነው፡፡ ብዙ ጊዜ የመልሶ ማልማት ሂደቶች ተገቢ የሆነ የከተማ ዲዛይን ሳይኖራቸው ይካሄዳሉ፡፡ ለዚህም ነው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባዶ ቦታዎችን (ፀጥታን) እና ሕንፃዎችን (ጫጫታን) ለማስታረቅ የሚሞክር ዲዛይን ጉዳይ መነጋገሪያ የሆነው፡፡

በ2004 ዓ.ም የኢትዮጵያ የአርኪቴክቸር ሕንጻ ግንባታና ከተማ ፕላን ኢንስቲትዩት (EiABC)፣ በተለምዶ ባሻ ወልዴ ችሎት ተብሎ ለሚጠራው አካባቢ ተገቢ የሆነ የከተማ ዲዛይን ሠርቶ ነበር፡፡ መጀመሪያ ባዶ ቦታዎቹ፣ ቀጥሎ ሕንፃዎቹ ባዶ ቦታዎቹን በሚወስኑ መልኩ ዲዛይን መደረጋቸው ፕሮጀክቱን ከተለመደው ልዩ ያደርገዋል፡፡ ዙርያ-ገጠም ጥምር ሕንጻ (Perimeter block) በመጠቀም ባዶ ቦታዎቹ እና መንገዶቹ እንዲወሰኑ ተደርጓል፡፡ ሕንፃዎቹን የሚመጣጠን የባዶ ቦታዎች መርበብ ተፈጥሯል፡፡ ከዚህ በተቃራኒው ከላይ እንደተገለጸው አብዛኛው የከተማው የመልሶ ማልማት ፕሮጀክት ትኩረት በሕንፃዎች ዲዛይን ላይ ነው፡፡ በየሕንፃዎቹ መካከል ያሉ ክፍት ቦታዎች ለዕድል በመተዋቸው ምክንያት፣ ሰዎች በሕገወጥነት ከይዞታቸው ጋር ይጠቀልሏቸዋል፤ ወይም የቆሻሻ መጣያ ይሆናሉ፤ ወይንም ለሌላ ላልተገባ ዓላማ ይውላሉ፡፡

አዲስ አበባ ለኖዋሪዎቿ ምቹ መሆን ካለባት ከዩቫስኪላ ከተማ ስለ ፀጥታና ባዶ ቦታዎች ምንነትና ጥቅም መማር ይኖርባታል፡፡ ከተማዋ የሕዝብ ቦታዎችንና መናፈሻዎችን ቁጥር ማሳደግን ጊዜ ልትሰጠው አይገባም፡፡ የሕንፃዎችና አካባቢያቸው ጫጫታ በባዶ ቦታዎች አቅርቦትና ዝምታ ሚዛኑን ካልጠበቀ ከተማዋ የኮንክሪት ጫካ ሆና ልትቀር ትችላለች፡፡ ዩቫስኪላም በበኩሏ ሰፊ ዝምታዋንና አሰልቺ የሕይወት ዑደቷን ለማመጣጠን የአዲስ አበባን ሕይወታማ የጎዳና ላይ እንቅስቃሴና ግብታዊነት ሊያስፈልጋት ይችላል፡፡ በፊንላንድ ውስጥ ለትዳር ፍቺ ከሆኑት ምክንያቶች አንዱ በባልና ሚስት መካከል በቂ ውይይት ያለመኖር መሆኑ ይነገራል፡፡ ግልጽ የሆነ ነገር መግለጫ አያስፈልገውም የሚለው እሳቤ ውይይትን በማቀጨጭ ትዳርን እስከማፍረስ ሊያደርስ ይችላል፡፡ ሆኖም የውይይቱ ቁጥብ የመሆን ምክንያት የመረጃ ድግግሞሽን ለማስወገድና ግልጽ (የሚታወቅ) ነገርን በመናገር ቃላትን ላለማባከን በማሰብ መሆኑን አውቃለሁ፡፡ አንድ ፊንላንዳዊ ወዳጄ ይህንን ለማስረዳት የሚከተለውን ታሪክ አጫውቶኛል፡፡


አንድ ሽማግሌ አድራሻውን የማያውቁትን ቦታ ለመጎብኘት ፈልገው፣ ወደ ወዳጃቸው ቤት በመሄድ ቦታውን የሚያሳያቸው ልጅ እንዲሰጣቸው ጠየቁ፡፡ የቤቱ እመቤትም ልጃቸው ከሽማግሌው ጋር በመሄድ ቦታውን እንዲያሳያቸው ፈቀዱ፡፡ ሽማግሌውና ወጣቱ ልጅ ወደ ተፈለገው ቦታ ጉዟቸውን  መሩ፡፡ ሁለቱም አንድም ቃል ሳይተነፍሱ በዝምታ ጉዟቸውን ተያያዙት፡፡ ረዥም መንገድ ከተጓዙ በኋላ ወጣቱ ከባድ ደመና አዝሎ የጠቆረውን ሰማይ በመመልከት “ሊዘንብ ነው መሰለኝ” በማለት ተናገረ፡፡ ሆኖም ከሽማግሌው ምንም መልስ አላገኘም፡፡ ትንሽ ከተጓዙ በኋላ ወዳሰቡበት ቦታ ደረሱ፡፡ ሽማግሌው የፈለጉትን ቦታ ከጎበኙ በኋላ ወደ ቤት መመለስ  መሩ፡፡ በመልስ ጉዟቸውም ያንን ያህል ረዥም መንገድ ሲጓዙ ምንም አልተጨዋወቱም፡፡ በጉዞው ሙሉ የነበረው ንግግር ቅድም ልጁ ስለዝናቡ የሰነዘረው ሐሳብ ብቻ ነበር፡፡ በመጨረሻ የልጁ ቤት ሲደርሱ ሽማግሌው የልጁን እናት እንዲህ አሏቸው፡፡ “ጎበዝ ልጅ አለሽ ግን ብዙ ያወራል”

ፊንላንዳዊው ጓደኛዬ ቀጠል በማድረግ “አየህ እኛ ስለማንናገር ሳይሆን፣ ግልጽ የሆነውንና ተደጋጋሚ የሆነ ንግግርን በተቻለ መጠን ማስወገድ ስለምንፈልግ ነው፡፡ ነገሩ ግልጽ ሆኖ ሳለ ወጣቱ ልጅ ሊዘንብ ነው መሰለኝ ማለት ለምን አስፈለገው!” በማለት አብራራልኝ፡፡

እኔ እንደሚመስለኝ አዲስ አበባ ለዩቫስኪላ ትንሽ ጫጫታና ሰው ሰራሽ ቁሶች ብታጋራት፣ ዩቫስኪላ ደግሞ ለአዲስ አበባ ትንሽ ፀጥታና ባዶ ቦታዎች ብትለግሳት መልካም ነበር፡፡ አዲስ አበባ ተጨማሪ እርጋታና ማሰላሰል ዩቫስኪላ ደግሞ ተጨማሪ መነቃቃትና እንቅስቃሴ ያስፈልጋቸዋል፡፡

ከቁሳቁስና እንቅስቃሴ ይልቅ ፀጥታ ይበልጣል በማለት ፅንፍ ይዘው ለሚከራከሩ ሰዎች ፣ እንደሚመስለኝ፣ ውይይትና አብረውን ከሚኖሩ ሰዎች ጋር የምናደርገው መስተጋብር የሰው ልጅ ባሕርያዊ ፍላጎት መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ የንጥረ ነገሮች የእርስ በእርስ ቁርኝት ማዕድናትን፣ ዕጽዋትን፣ እንስሳትንና ሰዎችን እንዲኖሩ ያረጋቸዋል፡፡ ቁርኝትና የእርስ በእርስ ግንኙነት ሕይወት ሲያመጣ፣ መነጠል ደግሞ ወደ ሞት መምራቱ የተፈጥሮ ሕግ ነው፡፡ አጠቃላይ በሆነ መልኩ የተሟላ ሕይወት ለመኖር ሰዎች ከመሰል ጎረቤቶቻቸው ጋር ጥብቅ መስታጋብር መፍጠር ይኖርባቸዋል፡፡ ተግባቦትና ማኅበራዊ ግንኙነት ቅንጦት ሳይሆን መሠረታዊ ፍላጎት ነው፤ ለሰዎች የጋራ ማንነት ባዕድ ሳይሆን ተፈጥሯዊ ባሕርይ ነው፡፡

ከዝምታ ይልቅ ቁሶች ይበልጣሉ በማለት ፅንፍ ይዘው ለሚከራከሩ ደግሞ እ.ኤ.አ በ1915 የተሰራውንና ከገላጭ ቁሶች ነፃ የሆነውን “The Black Square (ጥቁሩ አራት ማዕዘን)” በመባል የሚታወቀውን የካዝሚር ማለቪች ቀለም ቅብ በተመለከተ አንድሩ ግርሃም ዲክሰን በቢቢሲ ዶክዩመንታሪ የተናገረውን ላጋራችሁ፡፡ “ወግ አጥባቂዎቹ በሥዕሉ ላይ ለመሳለቅ ሞከሩ፡፡ ማለቪች አብዷል፤ ጥቁሩ አራት ማዕዘንን የሳለው ጨለማ ውስጥ መሆን አለበት አሉ፡፡ የማሊቪች መልስ ቀጥተኛ ነበር፡፡ ‘እንደናንተ ባለመሆኔ ደስተኛ ነኝ፡፡ በረሃው ላይ አሁንም አሁንም ርቄ መሄድ እችላለሁ፤ መቀየር የሚገኘው እዛ ነውና፡፡ የኔ ጥቁሩ አራት ማዕዘን፣ ሌጣና መቃን አልባ የዘመናችን መገለጫ ነው፡፡ ተነሱ ጓዶች ራሳችሁን በቁሶች ከመገዛት ነፃ አውጡ!”

a, .uk-link { color: #c66322; text-decoration: none; cursor: pointer; }